ዘፀአት 10

የአንበጣ መንጋ መቅሠፍት

1 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤

2 ይኸውም ግብፃውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔእግዚአብሔር(ያህዌ)መሆኔንም እንድታውቁ ነው።”

3 ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እምቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው።

4 እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ።

5 አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል።

6 የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብፃውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።

7 የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውንእግዚአብሔርን(ያህዌ)እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብፅ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን? አሉት።

8 ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁንእግዚአብሔርን(ያህዌ)አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ።

9 ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር(ያህዌ)በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።

10 ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር እንድትሄዱ እለቃችኋለሁእግዚአብሔር(ያህዌ)ከእናንተ ጋር ይሁን ነገር ግን ተንኰል አስባችኋል።

11 አይሆንም ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱናእግዚአብሔርን(ያህዌ)እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።

12 እግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብፅ አገር ላይ ዘርጋ” አለው።

13 ስለዚህ ሙሴ በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤እግዚአብሔርም(ያህዌ)በዚያን ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግሥቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ።

14 እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም።

15 ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ፣ ጠርገው በሉ። በግብፅ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።

16 ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁበእግዚአብሔር(ያህዌ)በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤

17 እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህንን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁንእግዚአብሔርን(ያህዌ)ለምኑልኝ።”

18 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደእግዚአብሔር(ያህዌ)ጸለየ።

19 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕርከተታቸው፤ በግብፅ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም።

20 እግዚአብሔር(ያህዌ)ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።

የጨለማ መቅሠፍት

21 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን፣ “በግብፅ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው።

22 ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብፅ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ።

23 በነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር።

24 ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁእግዚአብሔርን(ያህዌ)አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ አብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው።

25 ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችንለእግዚአብሔር(ያህዌ)መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤

26 እንስሶቻችን ሁሉ አብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳን አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችንለእግዚአብሔር(ያህዌ)አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊትእግዚአብሔርን(ያህዌ)ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።”

27 ነገር ግንእግዚአብሔር(ያህዌ)የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም።

28 ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ስማ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው።

29 ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን! እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *