እግዚአብሔር ይመጣል፤ ይነግሣልም
1 እነሆ፤የእግዚአብሔርቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ።
2 ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም።
3 እግዚአብሔርምበጦርነት ጊዜ እንደሚ ዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል።
4 በዚያን ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤
5 እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬእግዚአብሔርይመጣል፤ ቅሆሳኑም ሁሉ አብረውት ይመጣሉ።
6 በዚያ ቀን በረዶ ውርጭና ብርሃን አይኖርም።
7 ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀንበእግዚአብሔርየታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።
8 በዚያን ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕርይፈሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።
9 እግዚአብሔርበምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያን ቀንእግዚአብሔርአንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።
10 ምድር ሁሉ ከጌባ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሬሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።
11 የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች።
12 እግዚአብሔርኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጒድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ።
13 በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል።
14 ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል።
15 ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ይመታል።
16 ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ለእግዚአብሔርጸባኦት ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ።
17 የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ለእግዚአብሔርጸባኦት ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም።
18 የግብፅም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤እግዚአብሔርወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል።
19 የዳስን በዓል ወጥተው ለማያከብሩ ግብፃውያንና አሕዛብ ሁሉ የተወሰነው ቅጣት ይህ ነው።
20 በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፣ “ቅዱስለእግዚአብሔር” የሚል ጽሑፍ ይቀረጻል፤ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የማብሰያ ምንቸቶች ከመሠዊያው ፊት ለፊት እንዳሉ ሳሕኖች የተቀደሱ ይሆናሉ።
21 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸባኦት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡ ሁሉ ምንቸቶቹን በመውሰድ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ቀንበእግዚአብሔርጸባኦት ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ከነዓናዊአይገኝም።