ዘካርያስ 12

የኢየሩሳሌም ጠላቶች እንደሚደመሰሱ የተነገረ ንግር

1 ስለ እስራኤል የተነገረውየእግዚአብሔርቃል ይህ ነው፤ ሰማያትን የዘረጋ፣ ምድርን የመሠረተ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

2 “ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሚያንገደግድ ጽዋ አደርጋታለሁ፤ ይሁዳም እንደ ኢየሩሳሌም ሁሉ ትከበባለች።

3 የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሷ ላይ በሚሰበሰቡበት በዚያ ቀን፣ ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ የማይነቃነቅ ዐለት አደርጋታለሁ፤ ለማነቃነቅ የሚሞክሩ ሁሉ ራሳቸውን ይጐዳሉ።

4 በዚያን ቀን እያንዳንዱን ፈረስ በድንጋጤ፣ የተቀመጡባቸውንም ሰዎች እብደት እመታለሁ” ይላልእግዚአብሔር። “የይሁዳን ቤት በዐይኔ እጠብቃለሁ፤ ነገር ግን የአሕዛብን ፈረሶች ሁሉ አሳውራለሁ።

5 የይሁዳ መሪዎች በልባቸው፣ ‘የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ብርቱ ናቸው፤ አምላካቸውእግዚአብሔርጸባኦት ነውና’ ይላሉ።

6 “በዚያ ቀን የይሁዳን መሪዎች በዕንጨት ክምር ውስጥ እንዳለ የእሳት ምድጃ፣ በነዶም መካከል እንዳለ የፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በግራና በቀኝ ዙሪያውን ያሉትን ሕዝቦች ይበላሉ፤ ኢየሩሳሌም ግን ከስፍራዋ ንቅንቅ አትልም።

7 “የዳዊት ቤትና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር ከይሁዳ ክብር እንዳይበልጥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የይሁዳን መኖሪያዎች ያድናል።

8 ከመካከላቸው እጅግ ደካማ የሆነው እንደ ዳዊት፣ የዳዊት ቤትምፊት ፊታቸው እንደሚሄድ እንደእግዚአብሔርመልአክ፣ እንደ አምላክ ይሆንላቸው ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትንእግዚአብሔርይከልላቸዋል።

9 በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን በወጓት አሕዛብ ሁሉ ላይ እወጣለሁ።

ስለ ወጉት የተደረገ ሐዘን

10 “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የልመና መንፈስ አፈሳለሁ፤ ወደ ወጉኝ ወደእኔም ይመለከታሉ፤ እነርሱም ለአንድያ ልጅ እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኵር ልጅ ምርር ተብሎ እንደሚለቀስም አምርረው ያለቅሱለታል።”

11 በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ ለሐዳድሪሞን እንደተለቀሰ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚለቀሰውም እንደዚሁ ታላቅ ልቅሶ ይሆናል።

12 ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ የየነገዱ ወንዶች ለየራሳቸው ያለቅሳሉ፤ ሚስቶቻቸውም ለየራሳቸው ያለቅሳሉ፤ በዚህም ዐይነት የዳዊት ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣ የናታን ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣

13 የሌዊ ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣ የሰሜኢ ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣

14 የቀሩትም ነገዶች ወንዶች ሁሉ ከነሚስቶቻቸው ያለቅሳሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *