ቃል የተገባው የአዲሱ ቤት ክብር
1 በሰባተኛው ወር፣ በሃያ አንደኛ ቀንየእግዚአብሔርቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤
2 “ለይሁዳ ገዥ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፣ ለሊቀ ካህናቱ ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፣ ከምርኮ ለተረፈውም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ጠይቃቸው፤
3 ‘ይህን ቤት በቀድሞ ክብሩ ሳለ ያየ ከመካከላችሁ ማን አለ? አሁንስ ምን መስሎ ይታያችኋል? ይህ በፊታችሁ ምንም እንዳይደለ የሚቈጠር አይደለምን?
4 እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላልእግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔር፤
5 ‘ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ የገባ ሁላችሁ ቃል ይህ ነው፤ መንፈሴም በመካከላችሁ ይሆናልና አትፍሩ።’
6 “ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በቅርብ ጊዜ እንደ ገና ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን አንድ ጊዜ አናውጣለሁ።
7 ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔር።
8 ‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔርጸባኦት፤
9 ‘የዚህ የአሁኑ ቤት ክብር ከቀድሞው ቤት ክብር ይበልጣል’ ይላል ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔርጸባኦት፤ ‘በዚህም ቦታ ሰላምን እሰጣለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔርጸባኦት።”
ተግሣጽና በረከት
10 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀንየእግዚአብሔርቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤
11 “እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ሕጉምን እንደሚል ካህናቱን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፤
12 አንድ ሰው የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፣ ያም ዕጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይም ሌላ ምግብ ቢነካ የተቀደሰ ይሆናልን?”
ካህናቱም፣ “የተቀደሰ አይሆንም” ብለው መለሱ።
13 ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው፣ ከእነዚህ አንዱን ቢነካ፣ የተነካው ነገር ይረክሳልን?” ሲል ጠየቀ።
ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳል” ሲሉ መለሱ።
14 ከዚያም ሐጌ እንዲህ አለ፤ “ ‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላልእግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው’።
15 “ ‘እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁበእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስተውሉ።
16 አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደ ሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ አምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ፤
17 የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላልእግዚአብሔር፤
18 ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮየእግዚአብሔርቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤
19 በጐተራ የቀረ ዘር አሁንም ይገኛልን? የወይኑና የበለሱ ዛፍ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ እስካሁን አላፈሩም።
“ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’ ”
እግዚአብሔር ለዘሩባቤል የሰጠው ተስፋ
20 በወሩ ሃያ አራተኛ ቀንየእግዚአብሔርቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፤
21 “ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል ሰማያትንና ምድርን እንደማናውጥ ንገረው፤
22 የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል አጠፋለሁ፤ ሠረገሎችንና ሠረገለኞችን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውም በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።
23 “ ‘እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በዚያን ቀን ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፤ እኔ እወስድሃለሁ’ ይላልእግዚአብሔር፤ ‘እንደ ማተሚያ ቀለበቴ አደርግሃለሁ፤ እኔ መርጬአለሁና’ ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።”