የዮናስ ጸሎት
1 ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደእግዚአብሔርጸለየ፤
2 እንዲህም አለ፤
“ተጨንቄ ሳለሁ ወደእግዚአብሔርተጣራሁ፤
እርሱም መለሰልኝ፤
ከመቃብሩምጥልቅ ርዳታን ፈልጌ ተጣራሁ፤
አንተም ጩኸቴን ሰማህ።
3 ጥልቅ ወደ ሆነው፣
ወደ ባሕሩ መካከል ጣልኸኝ፤
ፈሳሾችም ዙሪያዬን ከበቡኝ፤
ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ፣
በላዬ አለፉ።
4 እኔም፣ ‘ከፊትህ ጠፋሁ፣
ነገር ግን እንደ ገና፣
ወደ ቅዱስ መቅደስህ፣
እመለከታለሁ’ አልሁ።
5 ውሃ እስከ ዐንገቴ አጠለቀኝ፤
ጥልቁም ከበበኝ፤
የባሕርም ዐረም በራሴ ላይ ተጠመጠመ።
6 ወደ ተራሮች መሠረት ሰመጥሁ፤
የምድርም በር ለዘላለም ተዘጋብኝ፤
እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤
አንተ ግን ሕይወቴን ከጒድጓድ አወጣህ።
7 “ነፍሴ በዛለች ጊዜ፣
እግዚአብሔርሆይ፤ አንተን ዐሰብሁ፤
ጸሎቴም ወደ አንተ፣
ወደ ቅዱስ መቅደስህ ዐረገች።
8 “ከንቱ በሆኑ ጣዖቶች ላይ የሚንጠለጠሉ፤
ሊያገኙ የሚገባቸውን ጸጋ ያጣሉ።
9 እኔ ግን በምስጋና መዝሙር፣
መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤
የተሳልሁትንም እሰጣለሁ፤
ድነትከእግዚአብሔርዘንድ ነው።”
10 እግዚአብሔርምዓሣውን አዘዘው፤ ዮናስንም በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።