አሞጽ 9

እስራኤል ትጠፋለች

1 ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፤

“መድረኮቹ እንዲናወጡ፣

ጒልላቶቹን ምታ፣

በሕዝቡም ሁሉ ራስ ላይ ሰባብራቸው፤

የቀሩትን በሰይፍ እገድላቸዋለሁ፤

ከእነርሱ አንድም ሰው አይሸሽም፤

ቢሸሽም የሚያመልጥ የለም።

2 መቃብርበጥልቀት ቈፍረው ቢወርዱም፣

እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤

ወደ ሰማይ ቢወጡም፣

ከዚያ አወርዳቸዋለሁ።

3 በቀርሜሎስ ጫፍ ላይ ቢሸሸጉም፣

አድኜ ፈልጌ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤

እይዛቸዋለሁም፤

በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከእኔ ቢሸሸጉም፣

በዚያ እባቡ እንዲነድፋቸው አዘዋለሁ፤

4 በጠላቶቻቸው ተነድተው ለምርኮ ቢወሰዱም፣

በዚያ እንዲገድላቸው ሰይፍን አዛለሁ፤

ለመልካም ሳይሆን ለክፉ፣

ዓይኔን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ።

5 ጌታ፣እግዚአብሔርጸባኦት፣

ምድርን ይዳስሳል፤

እርሷም ትቀልጣለች፤

በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤

የምድር ሁለመና እንደ ዐባይ ወንዝ ይነሣል፤

እንደ ግብጽ ወንዝም ይወርዳል።

6 መኖሪያውንበሰማይ የሚሠራ፣

መሠረቱንምበምድር የሚያደርግ፣

የባሕርን ውሃ የሚጠራ፣

በምድርም ገጽ ላይ የሚያፈስ፣

እርሱ ስሙእግዚአብሔርነው።

7 “እናንት እስራኤላውያን፣

ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?”

ይላልእግዚአብሔር

“እስራኤልን ከግብጽ፣

ፍልስጥኤማውያንን ከከፍቶር፣

ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?

8 “እነሆ፤ የጌታእግዚአብሔርዐይኖች፣

በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤

ከምድር ገጽ፣ ፈጽሜ አጠፋዋለሁ፤

የያዕቆብን ቤት ግን፣ ሙሉ በሙሉ

አልደመስስም፤”

ይላልእግዚአብሔር።

9 “እነሆ፤ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤

እህል በወንፊት እንደሚነፋ፣

የእስራኤልን ቤት፣

በሕዝብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤

ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።

10 በሕዝቤ መካከል ያሉ፣

‘ክፉ ነገር አያገኘንም ወይም አይደርስብንም’ የሚሉ፣

ኀጢአተኞች ሁሉ፣

በሰይፍ ይሞታሉ።

የእስራኤል መመለስ

11 “በዚያ ቀን፣

የወደቀውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፤

የተሰበረውን እጠግናለሁ፤

የፈረሰውን ዐድሳለሁ፤

ቀድሞ እንደነበረም አድርጌ እሠራዋለሁ፤

12 ስለዚህ የኤዶምን ትሩፍ፣

በስሜየተጠሩትንም ሕዝቦች ሁሉ ይወርሳሉ፤”

ይላል ይህን የሚያደርግእግዚአብሔር።

13 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ ዐጫጁ ዐጭዶ ሳይጨርስ፣

ዐራሹ በላዩ የሚደርስበት፣

ችግኝ ተካዩም ገና ተክሎ ሳይጨርስ፣

ወይን ጨማቂው የሚደርስበት ጊዜ ይመጣል፤

አዲስ የወይን ጠጅ ከተራሮች ይንጠባጠባል፤

ከኰረብቶችም ሁሉ ይፈሳል።

14 የተሰደደውንሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ፤

እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ።

የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤

አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።

15 እስራኤልን በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤

ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛ

አይነቀሉም”

ይላል አምላክህእግዚአብሔር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *