አሞጽ 5

የእስራኤል ሕዝብ ለንስሓ መጠራት

1 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ የምደረድረውን ይህን የሙሾ ቃል ስሙ፤

2 “ድንግሊቱ እስራኤል ወደቀች፤

ከእንግዲህም አትነሣም፤

በገዛ ምድሯ ተጣለች፤

የሚያነሣትም የለም።”

3 ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“አንድ ሺህ ብርቱዎችን ለእስራኤል የምታዘምት ከተማ፣

አንድ መቶ ብቻ ይቀሯታል፤

አንድ መቶ ብርቱዎችን የምታዘምተውም፣

ዐሥር ብቻ ይቀሯታል።”

4 እግዚአብሔርለእስራኤል ቤት እንዲህ

ይላል፤ “እኔን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።”

5 ቤቴልን አትፈልጉ፤

ወደ ጌልገላ አትሂዱ፤

ወደ ቤርሳቤህም አትሻገሩ፤

ጌልገላ በእርግጥ ትማረካለች፤

ቤቴልም እንዳልነበረችትሆናለችና።

6 እግዚአብሔርንፈልጉ፤

በሕይወትም ትኖራላችሁ፤

አለበለዚያ እንደ እሳት የዮሴፍን ቤት ያወድማል፤

እሳቱም ቤቴልን ይበላል፤ የሚያጠፋውም የለም።

7 እናንት ፍትሕን ወደ መራርነት የምትለውጡ፣

ጽድቅንም ወደ ምድር የምትጥሉ ወዮላችሁ!

8 ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮንን የሠራ፣

ጨለማውን ወደ ንጋት ብርሃን የሚለውጥ፣

ቀኑን አጨልሞ ሌሊት የሚያደርግ፣

የባሕሩንም ውሃ ጠርቶ፣

በገጸ ምድር ላይ የሚያፈስ፣

ስሙ እግዚአብሔር ነው፤

9 እርሱ በብርቱው ላይ ድንገተኛ ጥፋትን፣

በተመሸገውም ከተማ ላይ ውድመትን ያመጣል።

10 እናንተ በፍርድ አደባባይ

የሚገሥጻችሁን ትጠላላችሁ፤ እውነት የሚናገረውንም ትንቃላችሁ።

11 እናንተ ድኻውን ትረግጣላችሁ፤

እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤

ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣

በውስጡ ግን አትኖሩም፤

ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣

የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤

12 ኀጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደሆነ፣

በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና።

ጻድቁን ትጨቊናላችሁ፤

ጒቦም ትቀበላላችሁ፤

በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።

13 ስለዚህ አስተዋይ ሰው በእንዲህ ያለ ጊዜ ዝም ይላል፤

ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና።

14 በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፣

መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤

ከዚያ በኋላ እንደ ተናገራችሁት፣

የሰራዊት አምላክእግዚአብሔርከእናንተ ጋር ይሆናል።

15 ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤

በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤

ምናልባትም የሰራዊት አምላክእግዚአብሔር፣

ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።

16 ስለዚህ ጌታ የሰራዊት አምላክ

እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“በየመንገዱ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤

በአደባባዩም የሥቃይ ጩኸት ይሆናል፤ ገበሬዎች ለልቅሶ፣

አልቃሾችም ለዋይታ ይጠራሉ።

17 በየወይኑ ዕርሻ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤

እኔ በመካከላችሁ አልፋለሁና፤”

ይላልእግዚአብሔር።

የእግዚአብሔር ቀን

18 የእግዚአብሔርንቀን ለምትሹ፣

ለእናንተ ወዮላችሁ

የእግዚአብሔርንቀን ለምን ትሻላችሁ?

ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።

19 ይህ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሲሸሽ፣

ድብ እንደሚያጋጥመው፣

ወደ ቤቱም ገብቶ፣ እጁን በግድግዳው

ላይ ሲያሳርፍ፣

እባብ እንደሚነድፈው ነው።

20 የእግዚአብሔርቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ፣

የብርሃን ጸዳል የሌለው ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?

21 “ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤

ጠልቼውማለሁ፤ ጉባኤዎቻችሁ ደስ አያሰኙኝም።

22 የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ብታቀርቡልኝም፣

እኔ አልቀበለውም፤

ከሰቡ እንስሶቻችሁ የኅብረት መሥዋዕትብታቀርቡልኝም፣

እኔ አልመለከተውም።

23 የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤

የበገናህንም ዜማ አልሰማም።

24 ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣

ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።

25 “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣

መሥዋዕትንና ቊርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን?

26 ለራሳችሁ የሠራችሁትን፣

የንጉሣችሁን ቤተ ጣዖት፣

የጣዖቶቻችሁን ዐምድ፣

የአምላካችሁንኮከብ አንሥታችሁ ተሸከማችሁ።

27 ስለዚህ ከደማስቆ ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋችኋለሁ፤”

ይላል ስሙ የሰራዊት አምላክ የሆነእግዚአብሔር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *