የተፈረደባቸው ሕዝቦች
1 በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣
የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣
2 አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤
ወደ ኢዮሣፍጥምሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤
ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣
በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤
ምድሬን ከፋፍለዋል፤
ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና።
3 በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤
ወንዶች ልጆችን በዝሙት አዳሪዎች ለወጡ፤
ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣
ሴቶች ልጆችን ሸጡ።
4 “ጢሮስና ሲዶና እንዲሁም እናንተ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሁሉ ሆይ፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ምን አላችሁ? ስላደረግሁት ነገር ብድር ልትመልሱልኝ ነውን? የምትመልሱልኝ ከሆነ፣ በፍጥነትና በችኰላ እናንተ ያደረጋችሁትን በራሳችሁ ላይ መልሼ አደርግባችኋለሁ።
5 ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤ የተመረጠውንም ንብረቴን ተሸክማችሁ ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አስገብታችኋልና።
6 ከገዛ ምድራቸው ልታርቋቸው፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለግሪኮች ሸጣችኋቸው።
7 “እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ።
8 ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሰዎች ሸጣለሁ፤ እነርሱም መልሰው በሩቅ ላሉት ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤”እግዚአብሔርይህን ተናግሮአልና።
9 በሕዝቦች መካከል ይህን ዐውጁ፤
ለጦርነት ተዘጋጁ፤
ተዋጊዎችን አነሣሡ፤
ጦረኞችም ሁሉ ቀርበው ያጥቁ።
10 ማረሻችሁ ሰይፍ፣
ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት፤
ደካማውም ሰው፣
“እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።
11 እናንት በዙሪያ ያላችሁ ሕዝቦች ሁላችሁ፤
ፈጥናችሁ ኑ፤ በዚያም ተሰብሰቡ።
እግዚአብሔርሆይ፤ ተዋጊዎችህን ወደዚያ አውርድ!
12 “ሕዝቦች ይነሡ፤
ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ ፈጥነው ይውረዱ፤
ዙሪያውን ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ላይ ልፈርድ፣
በዚያ እቀመጣለሁና።
13 ማጭዱን ስደዱ፤
መከሩ ደርሶአልና፤
ኑ ወይኑን ርገጡ፤
የወይን መጭመቂያው ሞልቶ፣
ከጒድጓዶቹም ተርፎ ፈሶአልና፤
ክፋታቸው እንደዚህ ታላቅ ነው።”
14 ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ፣
ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ ተሰብስቦአል፤
ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ፣
የእግዚአብሔርቀን ቀርቦአልና።
15 ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤
ከዋክብትም ከእንግዲህ አያበሩም።
16 እግዚአብሔርከጽዮን ጮኾ ይናገራል፤
ከኢየሩሳሌም ያንጐደጒዳል፤
ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤
እግዚአብሔርግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣
ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።
በረከት ለእግዚአብሔር ሕዝብ
17 “ከዚያም እኔ አምላካችሁእግዚአብሔር፣
በቅዱሱ ተራራዬ በጽዮን እንደምኖር ታውቃላችሁ፤
ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፤
ከእንግዲህም ወዲያ ባዕዳን አይወሯትም።
18 “በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤
ኰረብቶችም ወተት ያፈሳሉ፤
በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎችሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤
ከእግዚአብሔርቤት ምንጭ ይፈልቃል፤
የሰጢምን ሸለቆ ያጠጣል።
19 ግብፅ ባድማ፣
ኤዶምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤
በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ፣
በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ፈጽመዋልና።
20 ይሁዳ ለዘላለም፣
ኢየሩሳሌምም ለትውልድ ሁሉ መኖሪያ ትሆናለች፤
21 ደማቸውን እበቀላለሁ፤
በደለኛውንም ንጹሕ አላደርግም።”
እግዚአብሔርበጽዮን ይኖራል!