ሕዝቅኤል 29

በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት

1 በዐሥረኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥራ ሁለተኛው ቀንየእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን አዙር፤ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤

3 እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል።

“ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣

የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ።

“የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤

ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።

4 ነገር ግን በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፤

የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤

ቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁት ዓሦች ሁሉ ጋር፣

ከወንዞችህ ጐትቼ አወጣሃለሁ።

5 አንተንና በወንዞችህ ያለውን ዓሣ ሁሉ፣

በምድረ በዳ እጥላለሁ።

በገላጣ መሬት ላይ ትወድቃለህ፤

የሚሰበስብህ፣ የሚያነሣህም አይኖርም።

ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች፣

ምግብ እንድትሆን አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

6 ከዚያም በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።

“ ‘ለእስራኤል ቤት የሸምበቆ በትር ነበርህ፤

7 በእጃቸው ሲይዙህ ተሰንጥረህ ትከሻቸውን ወጋህ፤ ሲደገፉህም ተሰብረህ ጀርባቸውን አጐበጥህ።

8 “ ‘ስለዚህ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፤ ሰዎችህንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ።

9 ግብፅ ባድማና ምድረ በዳ ትሆናለች፤ ከዚያም እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።

“ ‘የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ እኔም ሠርቼዋለሁ” ብለሃልና፤

10 ስለዚህ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በወንዞችህ ላይ ተነሥቻለሁ፤ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል እስከ አስዋን ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ ወሰን ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ።

11 የሰው እግርም ሆነ የእንስሳ ኮቴ በውስጧ አያልፍም፤ እስከ አርባ ዓመት ማንም አይኖርባትም።

12 የግብፅን ምድር ከጠፉት ምድሮች መካከል እንደ አንዱ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከተሞቿም በፈራረሱት ከተሞች መካከል አርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብፃውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።

13 “ ‘ያም ሆኖ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ከአርባ ዓመት በኋላ ግብፃውያንን ከተበተኑበት አገሮች መካከል እሰበስባቸዋለሁ።

14 ከተማረኩበት አመጣቸዋለሁ፤ ወደ አባቶቻቸው ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ።

15 ከመንግሥታት ሁሉ አነስተኛ ትሆናለች፤ ከሌሎችም አሕዛብ በላይ ራሷን ከፍ ማድረግ አትችልም። እጅግ ደካማ አደርጋታለሁ፤ ስለዚህ ሌሎችን አሕዛብ እንደ ገና መግዛት አትችልም።

16 ግብፅ ከእንግዲህ ለእስራኤል ሕዝብ መታመኛ አትሆንም፤ ለርዳታ ወደ እርሷ ዘወር ባሉ ጊዜ ላደረጉት ኀጢአት ግን መታሰቢያ ትሆናለች። ከዚያም እኔ ጌታእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

17 በሃያ ሰባተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀንየእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

18 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አስቸጋሪ በሆነ ዘመቻ ሰራዊቱን በጢሮስ ላይ አንቀሳቀሰ፤ የሁሉም ራስ ተመልጦአል፤ የሁሉም ትከሻ ተልጧል፤ ይሁን እንጂ እርሱና ሰራዊቱ በጢሮስ ላይ ካደረጉት ዘመቻ ያተረፉት ነገር የለም።

19 ስለዚህ ልዑልእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ግብፅን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጣለሁ፤ ሀብቷን ሁሉ ያግዛል፤ ለሰራዊቱም ደመወዝ ይሆን ዘንድ ምድሪቱን ይበዘብዛል፤ ይመዘብራልም።

20 እርሱና ሰራዊቱ ለእኔ በመልፋታቸው፣ ግብፅን ለድካሙ ዋጋ ሰጥቼዋለሁ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።

21 “በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድአበቅላለሁ፤ በመካከላቸውም አፍህን እከፍታለሁ፤ ከዚያም እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ያውቃሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *