ዐመፀኛዪቱ እስራኤል
1 በሰባተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹየእግዚአብሔርንሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ።
2 የእግዚአብሔርምቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
3 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ሐሳቤን ልትጠይቁ መጣችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ ከእኔ ጠይቃችሁ እንድትረዱ አልፈቅድም’፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።’
4 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጽላቸው፤
5 እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፣ ለያዕቆብ ቤት ዘር እጄን አንሥቼ ማልሁላቸው፤ በግብፅም ራሴን ገለጥሁላቸው። እጄንም አንሥቼ፣ ‘እኔእግዚአብሔርአምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።
6 በዚያን ቀን፣ ከግብፅ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው።’
7 እኔም፣ ‘እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብፅ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔእግዚአብሔርአምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።
8 “ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብፅንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብፅ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።
9 ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብፅ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።
10 ስለዚህ ከግብፅ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው።
11 ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው።
12 ደግሞም እኔእግዚአብሔርእንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።
13 “ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።
14 ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።
15 ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤
16 ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋር ተጣብቆአልና።
17 እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም።
18 ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ።
19 እኔ እግዚአብሔርአምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ።
20 በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔእግዚአብሔርአምላካችሁ እንደሆንሁም ታውቃላችሁ።’
21 “ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር።
22 ነገር ግን ከግብፅ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ።
23 ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤
24 ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋር ተጣብቆአል።
25 እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤
26 እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’
27 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እኔን በመተው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤
28 ልሰጣቸው ወደማልሁላቸው ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉና የለመለመውን ዛፍ ሁሉ ተመለከቱ፤ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ ቍርባናቸውን በማቅረብ ቍጣዬን አነሣሡ፤ መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣናቸውን ዐጠኑ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውንም አፈሰሱ።”
29 እኔም፣ ‘የምትሄዱበት ይህ ከፍታ ቦታ ምንድን ነው?” አልኋቸው።’ እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማተብሎ ይጠራል።
ቅጣትና ምሕረት
30 “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እንዳደረጉት ራሳችሁን ታረክሳላችሁን? በረከሱ ምስሎቻቸው ምኞት ትቃጠላላችሁን?
31 ቍርባናችሁን በምታቀርቡበት ጊዜ ልጆቻችሁን ለእሳት በመዳረግእስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ሁሉ እየረከሳችሁ ናችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ታዲያ የእኔን ሐሳብ እንድትጠይቁ ልፍቀድላች ሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።”
32 “ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም።
33 በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታእግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ።
34 ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ።
35 ወደ አሕዛብ ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ።
36 በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋር እፋረዳለሁ ይላል ጌታእግዚአብሔር።
37 ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋር አጣብቃችኋለሁ።
38 በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
39 “ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖታቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።
40 በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋር በዚያ እሻለሁ።
41 ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበ ሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።
42 ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
43 በዚያም መንገዳችሁንና ራሳችሁን ያረከሳችሁበትን ተግባር ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በፈጸማችሁትም ክፋት ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
44 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ብልሹ ተግባራችሁ ሳይሆን፣ ስለ ስሜ ስል በምጐበኛችሁ ጊዜ እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ይላል ጌታእግዚአብሔር።’ ”
በደቡቡ አገር ላይ የተነገረ ትንቢት
45 የእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
46 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ደቡብ አዙር፤ በደቡብ ላይ ቃል ተናገር፤ በደቡብ አገር ደን ላይም ትንቢት ተንብይ።
47 ለደቡቡ ደን እንዲህ በል፤ ‘የእግዚአብሔርንቃል ስማ፤ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “በአንተ ላይ እሳት ልለኵስ ነው፤ እሳቱ የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍህን ሁሉ ይበላል፤ የሚንቦገቦገው ነበልባሉም አይጠፋም፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ያለውን ፊት ሁሉ ይለበልባል።
48 ሰው ሁሉ እኔእግዚአብሔርእንዳነደድሁት ያያል፤ የሚያጠፋውም የለም።’ ”
49 እኔም፤ “ጌታእግዚአብሔርሆይ፤ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፣ ‘ተምሳሌት ብቻ ይመስላል’ ይሉኛል” አልሁ።