1 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በፊትህ ያለውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላና ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ።
2 ስለዚህ አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም መጽሐፉን አጐረሠኝ።
3 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምሰጥህን ይህን ጥቅል መጽሐፍ ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ።
4 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው።
5 ወደ እስራኤል ቤት እንጂ፣ ንግግሩ ወደማይገባና ቋንቋው ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህም፤
6 ንግግራቸው ወደማይገባና ቋንቋቸው ወደማይታወቅ፣ ቃላቸውንም መረዳት ወደማይቻልህ ብዙ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ይሰሙህ ነበር።
7 ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለሆኑ ሊሰሙኝ አልፈለጉም፤ ስለዚህ የእስራኤል ቤት አንተንም አይሰሙህም።
8 እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ።
9 ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር ድንጋይ አደርገዋለሁ። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም እንኳ አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር።”
10 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የምነግርህን ቃል ሁሉ በጥንቃቄ አድምጥ፤ በልብህም ያዝ።
11 ተነሥተህም በምርኮ ወዳሉት ወገኖችህ ሄደህ ተናገራቸው፤ ቢሰሙህም ባይሰሙህም፣ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል’ በላቸው።”
12 መንፈስም ወደ ላይ ከፍ አድርጎ አነሣኝ፤ ከኋላዬም ‘የእግዚአብሔርክብር በማደሪያ ስፍራው ይባረክ!’ የሚል ታላቅ ህምህምታ ሰማሁ፤
13 ይህም የሕያዋኑ ፍጡራን ክንፎች እርስ በርስ ሲጋጩና በአጠገባቸው ያሉት መንኰራኲሮች የሚያሰሙት ታላቅ ህምህምታ ነበር።
14 መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ወሰደኝ፤ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቊጣ ሄድሁ፤የእግዚአብሔርምጽኑ እጅ በላዬ ነበረች።
15 ከዚያም በኮቦር ወንዝ አጠገብ በቴልአቢብ ወደሚኖሩት ምርኮኞች መጣሁ፣ በድንጋጤ ፈዝዤም ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን በመካከላቸው ተቀመጥሁ።
ለእስራኤል የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
16 ከሰባቱም ቀን በኋላየእግዚአብሔርቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
17 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ ቃሌን ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው።
18 እኔ ኀጢአተኛውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ አንተ ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባትነግረው፣ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱይሞታል፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።
19 ነገር ግን ኀጢአተኛውን ሰው አስጠንቅቀኸው፣ ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ እርሱ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ።
20 “ጻድቁ ሰው ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ እኔም መሰናክል በፊቱ ባስቀምጥ እርሱ ይሞታል፤ አንተ አላስጠነ ቀቅኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረገውም ጽድቅ አይታሰብለትም፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።
21 ነገር ግን ጻድቁን ሰው ኀጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀውና እርሱም ኀጢአትን ባይሠራ፣ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን ታድናለህ።”
22 የእግዚአብሔርእጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ረባዳው ስፍራ ሂድ፤ በዚያ እናገርሃለሁ” አለኝ።
23 እኔም ተነሥቼ ወደ ረባዳው ስፍራ ሄድሁ። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየሁት ዐይነት ክብር፣የእግዚአብሔርክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ።
24 መንፈስ በውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እንዲህም ሲል ተናገረኝ፤ “ሂድ፤ ቤትህ ገብተህ በርህን ዝጋ።
25 አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ በገመድ ይጠፍሩሃል፤ ወጥተህም በሕዝብ መካከል እንዳትመላለስ ያስሩሃል።
26 ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ልትገሥጻቸው እንዳትችል ምላስህን ከላንቃህ ጋር አጣብቃለሁ፤ ድዳም ትሆናለህ።
27 ነገር ግን በምናገርህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ አንተም፣ ‘ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል’ ትላቸዋለህ። የሚሰማ ይስማ፤ የማይሰማም አይስማ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።