ኤርምያስ 48

ስለ ሞዓብ የተነገረ መልክት

1 ስለ ሞዓብ፤

የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ናባው ትጠፋለችና ወዮላት፤

ቂርያታይም ትዋረዳለች፤ ትያዛለችም፤

ምሽጎችይደፈራሉ፤ ይፈራርሳሉም።

2 ከእንግዲህ ሞዓብ አትከበርም፤

ሰዎች በሐሴቦንተቀምጠው፣

‘ኑ ያቺን አገር እናጥፋት’ ብለው ይዶልቱባታል።

መድሜንሆይ፤ አንቺም ደግሞ ጸጥ ትደረጊያለሽ፤

ሰይፍም ያሳድድሻል።

3 ከሖሮናይም የሚወጣውን ጩኸት፣

የመውደምና የታላቅ ጥፋት ድምፅ ስሙ!

4 ሞዓብ ትሰበራለች፤

ልጆቿም ጩኸት ያሰማሉ።

5 ክፉኛ እያለቀሱ፣

ወደ ሉሒት ሽቅብ ይወጣሉ፤

ስለ ደረሰባቸውም ጥፋት መራራ ጩኸት እያሰሙ፣

ወደ ሖርናይም ቍልቍል ይወርዳሉ።

6 ሽሹ፤ ሕይወታችሁንም አትርፉ!

በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦሁኑ።

7 በድርጊታችሁና በብልጽግናችሁ ስለምትታመኑ፣

እናንተም ትማረካላችሁ፣

ካሞሽም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋር፣

በምርኮ ይወሰዳል።

8 በእያንዳንዱ ከተማ ላይ አጥፊ ይመጣል፤

አንድም ከተማ አያመልጥም።

እግዚአብሔርተናግሮአልና፣

ሸለቆው ይጠፋል፤

ዐምባውም ይፈርሳል።

9 በራ እንድታመልጥ፣

ለሞዓብ ክንፍ ስጧት፤

ከተሞቿም ምንም እስከማይኖርባቸው ድረስ፣

ባድማይሆናሉ።

10 “የእግዚአብሔርንሥራ በቸልታ የሚያከናውን ርጉም ይሁን፤

ሰይፉን ደም ከማፍሰስ የሚከላከል የተረገመ ይሁን፤

11 “ሞዓብ በአምቡላው ላይ እንዳረፈ የወይን ጠጅ፣

ከልጅነት ጀምሮ የተረጋጋ ነበረ፤

ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤

በምርኮም አልተወሰደም፤

ቃናው እንዳለ ነው፤

መዐዛውም አልተለወጠም።

12 ስለዚህ ዕቃውን የሚገለብጡ ሰዎችን፤

የምልክበት ጊዜ ይመጣል፤”

ይላልእግዚአብሔር።

“እነርሱም ይደፉታል፤

ዕቃውን ባዶ ያስቀራሉ፤

ማንቆርቆሪያዎቹንም ይሰባብራሉ።

13 የእስራኤል ቤት፤

በቤቴል ታምኖ እንዳፈረ ሁሉ፣

ሞዓብም በካሞሽ ያፍራል።

14 “እናንተ፣ ‘እኛ ተዋጊዎች ነን፤

በጦርነትም ብርቱ ነን’ ልትሉ እንዴት ቻላችሁ?

15 ሞዓብ ትጠፋለች፤ ከተሞቿም ይወረራሉ፤

ምርጥ ወጣቶቿም ወደ መታረድ ይወርዳሉ፤”

ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርየሆነው ንጉሥ፤

16 “የሞዓብ ውድቀት ተቃርቦአል፤

ጥፋቱም ፈጥኖ ይመጣበታል።

17 በዙሪያው የምትኖሩ ሁሉ፤

ዝናውን የምታውቁ ሁሉ አልቅሱለት፤

‘ብርቱው ከዘራ፣

የከበረው በትር እንዴት ሊሰበር ቻለ’ በሉ።

18 “ሞዓብን የሚያጠፋ፣

በአንቺ ላይ ይመጣልና፤

የተመሸጉ ከተሞችሽንም ያጠፋልና፤

አንቺ የዲቦን ሴት ልጅ ሆይ፣

ከክብርሽ ውረጂ፣

በደረቅም መሬት ተቀመጪ።

19 አንቺ በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ፤

በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤

የሚሸሸውን ወንድ፣ የምታመልጠውንም ሴት፣

ምን ተፈጠረ?’ ብለሽ ጠይቂ።

20 ሞዓብ በመፍረሱ ተዋርዷል፤

ዋይ በሉ፤ ጩኹ፤

የሞዓብን መደምሰስ፣

በአርኖን አጠገብ አስታውቁ።

21 ፍርድ በዐምባው ምድር፦

በሖሎን፣ በያሳና በሜፍዓት ላይ፣

22 በዲቦን፣ በናባውና በቤት ዲብላታይም ላይ፣

23 በቂርያታይም፣ በቤት ጋሙልና በቤትምዖን ላይ፣

24 በቂርዮትና በባሶራ ላይ፤

በሩቅና በቅርብ፣ ባሉት በሞዓብ ከተሞች ሁሉ ላይ መጥቶአል።

25 የሞዓብ ቀንድተቈርጦአል፤

እጁም ተሰባብሮአል፤”

ይላልእግዚአብሔር።

26 “እግዚአብሔርንንቆአልና፣

ሞዓብን በመጠጥ አስክሩት።

ሞዓብ በትፋቱ ላይ ይንከባለል፤

ለመዘባበቻም ይሁን።

27 በእስራኤል ላይ ስታላግጥ አልነበረምን?

ስለ እርሷ በተናገርህ ቍጥር፣

እያቃለልሃት ራስህን የምትነቀንቀውስ፣

ከሌቦች ጋር ስትሰርቅ ተይዛለችን?

28 እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፤

ከከተማ ወጥታችሁ በዐለት መካከል ኑሩ፤

በገደል አፋፍ ላይ ጐጆዋን እንደምትሠራ፣

እንደ ርግብ ሁኑ።

29 “ስለ ሞዓብ ትዕቢት፣

ስለ እብሪቱና ስለ ኵራቱ፣

ስለ ትምክሕቱና ስለ መጓደዱ፣

ስለ ልቡም ማበጥ ሰምተናል።

30 መዳፉን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ከንቱ ነው፤”

ይላልእግዚአብሔር።

“ጒራውም ፋይዳ አይኖረውም።

31 ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ፤

ለሞዓብ ምድር ሁሉ ዋይ እላለሁ፤

ለቂርሔሬስ ሰዎችም የልቅሶ ድምፅ አሰማለሁ።

32 የሴባማ ወይን ሆይ፤

ለኢያዜር ካለቀስሁት እንኳ ይልቅ አለቅስልሻለሁ፤

ቅርንጫፎችሽ እስከ ባሕሩ ተዘርግተዋል፤

እስከ ኢያዜርም ደርሰዋል፤

ለመከር በደረሰው ፍሬሽና በወይንሽ ላይ፣

አጥፊው መጥቶአል።

33 ከሞዓብ የአትክልት ቦታና እርሻ፣

ሐሤትና ደስታ ርቆአል፤

የወይን ጠጅ ከመጭመቂያው እንዳይወርድ አድርቄዋለሁ፤

በእልልታ የሚጨምቀውም አይገኝም፤

በዚያ ድምፅ ቢሰማም፣

የእልልታ ድምፅ አይደለም።

34 “ከሐሴቦን እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ፣

ከዞዓር እስከ ሖሮናይም፣ እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ፣

ጩኸታቸው ከፍ ብሎ ይሰማል፤

የኔሞሬም ውሃ እንኳ ደርቆአልና።

35 በመስገጃ ኰረብቶች ላይ የሚሠዉትን፣

ለአማልክታቸው የሚያጥኑትን፣

ከሞዓብ አጠፋለሁ፤”

ይላልእግዚአብሔር፤

36 “ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ ዋሽንት ያንጐራጒራል፤

ለቂርሔሬስ ሰዎችም እንደ ዋሽንት ያንጐራጒራል።

ያከማቹት ንብረት ጠፍቶአልና።

37 የእያንዳንዱ ሰው ራስ፣

ጢምም ሁሉ ተላጭቶአል፤

እጅ ሁሉ ተቸፍችፎአል፤

ወገብም ሁሉ ማቅ ታጥቆአል።

38 በሞዓብ ቤቶች ጣራ ሁሉ ላይ፤፣

በሕዝብም አደባባዮች፣

ሐዘን እንጂ ሌላ የለም፤

እንደማይፈለግ እንስራ፣

ሞዓብን ሰብሬአለሁና፤”

ይላልእግዚአብሔር።

39 “እንዴት ተንኰታኰተ! ምንኛስ አለቀሱ!

ሞዓብ እንዴት ዐፍሮ ጀርባውን አዞረ!

ሞዓብ የመሰደቢያ፣

በዙሪያው ላሉትም ሁሉ የሽብር ምልክት ሆነ።”

40 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ እንደ ንስር ተወርውሮ ይወርድበታል፤

ክንፎቹንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል።

41 ከተሞቹይወረራሉ፤

ምሽጎቹም ይያዛሉ፤

በዚያን ቀን የሞዓብ ጦረኞች ልብ፣

በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ልብ ይሆናል።

42 ሞዓብእግዚአብሔርንአቃልሎአልና ይጠፋል፤

መንግሥትነቱም ይቀራል።

43 የሞዓብ ሕዝብ ሆይ፤

ሽብርና ጒድጓድ፣ ወጥመድም ይጠብቅሃል፤”

ይላልእግዚአብሔር።

44 “ከሽብር የሚሸሽ ሁሉ፣

ጒድጓድ ውስጥ ይገባል፤

ከጒድጓዱም የሚወጣ፣

በወጥመድ ይያዛል፤

በሞዓብ ላይ፣

የቅጣቱን ዓመት አመጣለሁና፣”

ይላልእግዚአብሔር፤

45 “የሞዓብን ግንባር፣

የደንፊዎችን ዐናት የሚያቃጥል፣

እሳት ከሐሴቦን፣

ነበልባል ከሴዎን ቤት ወጥቶአልና፤

ኰብላዮች በሐሴቦን ጥላ ሥር፣

ተስፋ ቈርጠው ቆመዋል።

46 ሞዓብ ሆይ፤ ወዮልህ!

የካሞሽ ሕዝብ ተደምስሶአል፤

ወንዶች ልጆችህ በምርኮ ተወስደዋል፤

ሴቶች ልጆችህም ተግዘዋል።

47 “ነገር ግን የኋላ ኋላ፣

የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፤”

ይላልእግዚአብሔር።

በሞዓብ ላይ የተወሰነው ፍርድ ይኸው ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *