መልካሙና መጥፎው በለስ
1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የኢዮአቄምን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንንናባለሥልጣኖቹን እንዲሁም የይሁዳን አናጺዎችና ብረት ቀጥቃጮች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው በኋላ፣እግዚአብሔርሁለት ቅርጫት በለስበእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ተቀምጦ አሳየኝ።
2 አንዱ ቅርጫት፣ ቶሎ የደረሰ ፍሬ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረበት፣ በሌላው ቅርጫት ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ የማይቻል እጅግ መጥፎ በለስ ነበረበት።
3 እግዚአብሔርም፣ “ኤርምያስ ሆይ፤ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ።
እኔም፣ “በለስን አያለሁ፤ ጥሩ የሆነው እጅግ መልካም ነው፤ የተበላሸው ግን እጅግ መጥፎ በመሆኑ ሊበላ የማይችል ነው” አልሁ።
4 እንደ ገናምየእግዚአብሔርቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
5 “የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ ከዚህ ስፍራ ወደ ባቢሎናውያንምድር የሰደድሁትን የይሁዳ ምርኮ በመልካም አስበዋለሁ።
6 ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
7 እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
8 “ ‘ነገር ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ እንደ ማይቻለው እንደ መጥፎ በለስ’ ይላልእግዚአብሔር፤ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና ባለሥልጣኖቹን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የቀሩትንም ሆነ በግብፅ የሚኖሩትን፣ እንዲሁ አደርግባቸዋለሁ።
9 በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉና የሚሰደቡ ይሆናሉ፤ በምበትናቸውም ስፍራ ሁሉ ለማላገጫና ለመተረቻ፣ ለመሣለቂያና ለርግማን አደርጋቸዋለሁ።
10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ ሰይፍ፣ ራብና መቅሠፍት እሰድባቸዋለሁ።