1 “የይሁዳ ኀጢአት በብረት ብርዕ፣
በሾለ የአልማዝ ጫፍ፣ ተጽፎአል፤
በልባቸው ጽላት፣
በመሠዊያቸውም ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል።
2 ልጆቻቸው እንኳ ሳይቀሩ፣
በለመለሙ ዛፎች ሥር፣
ከፍ ባሉ ኰረብቶችም ላይ ያሉትን፣
መሠዊያቸውንና አሼራ የተባለችውን ጣዖት ምስልያስባሉ።
3 በአገርህ ሁሉ ከተፈጸመው ኀጢአት የተነሣ፣
በምድሪቱ ያለህ ተራራዬ፣
ሀብትህንና ንብረትህን ሁሉ፣
መስገጃ ኰረብቶችህንም ጭምር፣
ለብዝበዛ አደርገዋለሁ።
4 በገዛ ጥፋትህ፣
የሰጠሁህን ርስት ታጣለህ፤
በማታውቀውም ምድር፣
ለጠላቶችህ ባሪያ አደርግሃለሁ፤
ለዘላለም የሚነደውን፣
የቍጣዬን እሳት ጭረሃልና።”
5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በሰው የሚታመን፣
በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣
ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።
6 በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤
መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤
ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣
በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል።
7 “ነገር ግንበእግዚአብሔርየሚታመን፣
መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8 በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣
ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣
ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤
ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤
በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤
ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”
9 የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤
ፈውስም የለውም፤
ማንስ ሊረዳው ይችላል?
10 “እኔእግዚአብሔርለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣
እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣
ልብን እመረምራለሁ፤
የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
11 ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣
ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤
በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤
በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል።
12 የመቅደሳችን ስፍራ፣
ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።
13 የእስራኤል ተስፋእግዚአብሔርሆይ፤
ጥለውህ የሚሄዱ ሁሉ ያፍራሉ፤
ፊታቸውን ከአንተ የሚመልሱ በምድር ውስጥ ይጻፋሉ፤
የሕይወትን ውሃ ምንጭ፣
እግዚአብሔርንትተዋልና።
14 እግዚአብሔርሆይ፤ ፈውሰኝ፤ እፈወሳለሁ፤
አድነኝ እኔም እድናለሁ፤
አንተ ምስጋናዬ ነህና።
15 እነርሱ ደጋግመው፣
“የእግዚአብሔርቃል የት አለ?
እስቲ አሁን ይፈጸም!” ይሉኛል።
16 እረኛ ሆኜ አንተን ከማገልገል ወደ ኋላ አላልሁም፤
ክፉ ቀን እንዳልተመኘሁ ታውቃለህ፤
ከአንደበቴ የሚወጣውም በፊትህ ግልጽ ነው።
17 አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤
በመከራ ቀን መሸሸጊያዬ አንተ ነህ።
18 አሳዳጆቼ ይፈሩ፤
እኔን ግን ከዕፍረት ጠብቀኝ፤
እነርሱ ይደንግጡ፤
እኔን ግን ከድንጋጤ ሰውረኝ፤
ክፉ ቀን አምጣባቸው፤
በዕጥፍ ድርብ ጥፋት አጥፋቸው።
ሰንበትን ማክበር
19 እግዚአብሔርእንዲህ አለኝ፤ “ሄደህ የይሁዳ ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ በር በሌሎቹም የኢየሩሳሌም በሮች ሁሉ ቁም፤
20 እንዲህም በላቸው፤ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ፤ የይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ፤የእግዚአብሔርንቃል ስሙ።
21 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳታስገቡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
22 አባቶቻችሁን እንዳዘዝኋቸው ሰንበትን አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ከየቤታችሁ ሸክም ይዛችሁ አትውጡ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ።”
23 እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ።
24 ነገር ግን በጥንቃቄ ብት ታዘዙኝ ይላልእግዚአብሔር፤ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ይዛችሁ ባትገቡ፣ የሰንበትንም ቀን ምንም ሳትሠሩ ብትቀድሱት፣
25 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መኳንንታቸው በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ በፈረሶችና በሠረገሎች ተቀምጠው በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ታጅበው ይመጣሉ፤ ይህቺም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች።
26 ሰዎች ከይሁዳ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ ከብንያምም አገር፣ ከቈላውና ከደጋው አገር እንዲሁም ከኔጌቭ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ ዕጣንና የምስጋና መሥዋዕት ይዘው ወደእግዚአብሔርቤት ይመጣሉ።
27 ነገር ግን የሰንበትን ቀን ሳትቀድሱ፣ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች በመግባት ትእዛዜን ብትጥሱ፣ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ምሽጎቿን የሚበላ፣ የማይጠፋ እሳት እጭራለሁ።”