1 እግዚአብሔርምእንዲህ አለኝ፤ “ሙሴና ሳሙኤል እንኳ በፊቴ ቢቆሙ፣ ልቤ ለዚህ ሕዝብ አይራራምና፤ ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ።
2 እነርሱም፣ ‘ወዴት እንሂድ?’ ቢሉህ፣ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ ‘ለሞት የተመደበ ወደ ሞት፣
ለሰይፍ የተመደበ ወደ ሰይፍ፣
ለራብ የተመደበ ወደ ራብ፣
ለምርኮ የተመደበ ወደ ምርኮ ይሄዳል።’
3 “እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘አራት ዐይነት አጥፊዎችን እሰድባቸዋለሁ፤ እነዚህም፦ ለመግደል ሰይፍ፣ ለመጐተት ውሾች፣ እንዲሁም ጠራርጎ ለመብላትና ለማጥፋት የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ናቸው።
4 የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ካደረገው በደል የተነሣ፣ ለምድር ነገሥታት ሁሉ መሰቀቂያ አደርጋቸዋለሁ።
5 “ኢየሩሳሌም ሆይ፤ የሚራራልሽ ማን ነው?
ማንስ ያለቅስልሻል?
ደኅንነትሽንስ ማን ጎራ ብሎ ይጠይቃል?
6 እኔን ጥለሽኛል” ይላልእግዚአብሔር፤
“ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤
ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤
ከእንግዲህም አልራራልሽም።
7 በአገሪቱ የከተማ ደጆች፣
በመንሽ እበትናቸዋለሁ፤
ከመንገዳቸው አልተመለሱምና፣
ሕዝቤን በሐዘን እመታለሁ፤
ጥፋትም አመጣባቸዋለሁ፤
8 የመበለቶቻቸውን ቍጥር፣
ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ፤
የጐበዛዝት እናቶች በሆኑትም ላይ፣
አጥፊውን በቀትር አመጣባቸዋለሁ።
ሽብርንና ድንጋጤን፣
በድንገት አወርድባቸዋለሁ።
9 የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤
ትንፋሿም ይጠፋል፤
ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤
እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤
የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣
ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤”
ይላልእግዚአብሔር።
10 ወይኔ እናቴ! ለምድር ሁሉ፣
የጭቅጭቅና የክርክር ሰው የሆንሁትን ምነው ወለድሽ!
ለማንም አላበደርሁም፤ ከማንም አልተበደርሁም፤
ነገር ግን ሰው ሁሉ ይረግመኛል።
11 እግዚአብሔርእንዲህ አለ፤
“በእርግጥ ለበጎ ዐላማ እታደግሃለሁ፤
በመከራና በጭንቅ ጊዜም፣
ጠላቶችህ ደጅ እንዲጠኑህ በእውነት አደርጋለሁ።
12 “ሰው ብረትን፣ ከሰሜን የመጣን ብረት፣
ነሐስንስ መስበር ይችላልን?
13 በመላ አገርህ፣
ስላለው ኀጢአትህ ሁሉ፣
ሀብትና ንብረትህን፣
ያለ ዋጋ አሳልፌ ለምርኮ እሰጣለሁ።
14 ቍጣዬ በላያችሁ፣
የሚነድ እሳት ትጭራለችና፣
በማታውቀው አገር፣
ለጠላቶችህባሪያ አደርግሃለሁ።”
15 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ታውቃለህ፤
እንግዲህ አስበኝ፤ ጐብኘኝም፤
አሳዳጆቼን ተበቀልልኝ።
ታጋሽ እንደ መሆንህ አታጥፋኝ፤
ባንተ ምክንያት የሚደርስብኝን ነቀፋ አስብ።
16 ቃልህ በተገኘ ጊዜ በላሁት፤
የሠራዊት አምላክእግዚአብሔርሆይ፤
በስምህ ተጠርቻለሁና፣
ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነልኝ።
17 ፈንጠዝያ ከሚያደርጉት ጋር አልተቀመጥሁም፤
ከእነርሱም ጋር አልፈነጨሁም፤
እጅህ በላዬ ስለ ነበር፣ በቍጣህ ስለ ሞላኸኝ፣
ለብቻዬ ተቀመጥሁ።
18 ሕመሜ ለምን ጸናብኝ?
ቍስሌስ ለምን በረታብኝ? ለምንስ የማይፈወስ ሆነ?
እንደሚያታልል ወንዝ፣
እንደሚያሳስት ምንጭ ትሆንብኛለህን?
19 ስለዚህእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ብትመለስ፣ መልሼ አቆምሃለሁ፤
ታገለግለኛለህም፤
የከበረውን ከማይረባው ለይተህ ብትናገር፣
አፍ ትሆነኛለህ፤
እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ እንጂ፣
አንተ ወደ እነርሱ አትመለስም፤
20 ለዚህ ሕዝብ የናስ ቅጥር፣ የተመሸገ
የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤
ልታደግህና፣ ላድንህም፣
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤
ቢዋጉህም እንኳ፣
ሊያሸንፉህ አይችሉም፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
21 “ከክፉዎች እጅ እቤዥሃለሁ፤
ከጨካኞችም ጭምደዳ እታደግሃለሁ።”