ፍርድና ተስፋ
1 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ሰማይ ዙፋኔ ነው፤
ምድርም የእግሬ ማረፊያ ናት፤
ታዲያ የምትሠሩልኝ ቤት፣
የማርፍበትስ ስፍራ የቱ ነው?
2 እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?
እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?”
ይላልእግዚአብሔር።
“ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣
ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣
በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
3 ነገር ግን ወይፈን የሚሰዋልኝ፣
ሰው እንደሚገድል ነው፤
የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣
የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤
የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣
የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤
የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣
ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤
የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤
ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል።
4 ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤
የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤
በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣
በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና።
በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤
የሚያስከፋኝንም መረጡ።”
5 እናንት በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣
ይህንየእግዚአብሔርቃል ስሙ፤
“እናንት ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣
ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣
‘እስቲእግዚአብሔርይክበርና፣
የእናንተን ደስታ እንይ’ አሏችሁ፤
ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።
6 ያን የጩኸት ድምፅ ከከተማው ስሙ!
ያን ጫጫታ ከቤተ መቅደሱ ስሙ!
ይኸውምየእግዚአብሔርድምፅ ነው፤
ለጠላቶቹም የሚገባቸውን ሁሉ ይከፍላቸዋል።
7 “ከማማጧ በፊት፣
ትወልዳለች፤
በምጥ ጣር ከመያዟ በፊት፣
ወንድ ልጅ ትገላገላለች።
8 እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል?
እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶ ያውቃል?
አገር በአንድ ጀምበር ይፈጠራልን?
ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል?
ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣
ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።
9 ሊወለድ የተቃረበውን፣
እንዳይወለድ አደርጋለሁን?” ይላልእግዚአብሔር።
“በሚገላገሉበት ጊዜስ፣
ማሕፀን እዘጋለሁን?” ይላል አምላክሽ።
10 “ወዳጆቿ የሆናችሁ ሁሉ፣
ከኢየሩሳሌም ጋር ደስ ይበላችሁ፤
ስለ እርሷም ሐሤት አድርጉ፤
ለእርሷ ያለቀሳችሁ ሁሉ፣
ከእርሷ ጋር እጅግ ደስ ይበላችሁ።
11 ከሚያጽናኑ ጡቶቿ፣
ትጠባላችሁ፤ ትረካላችሁም፤
እስክትረኩም ትጠጣላችሁ፤
በተትረፈረፈ ሀብቷም ትደሰታላችሁ።”
12 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ ሰላምን እንደ ወንዝ ውሃ አፈስላታለሁ፤
የመንግሥታትንም ብልጥግና እንደ ጅረት ውሃ አጐርፍላታለሁ፤
ትጠባላችሁ፤ በዕቅፏም ትያዛላችሁ፤
በጭኖቿም ላይ ትፈነድቃላችሁ።
13 እናት ልጇን እሹሩሩ እንደምትል፣
እኔም እናንተን እሹሩሩ እላችኋለሁ፤
በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ።
14 ይህን ስታዩ፣ ልባችሁ ሐሤት ያደርጋል፤
ዐጥንቶቻችሁም እንደ ሣር ይለመልማሉ፤
የእግዚአብሔርእጅ ከባሮቹ ጋር መሆኑ ይታወቃል፤
ቊጣው ግን በጠላቶቹ ላይ ይገለጣል።
15 እነሆ፤እግዚአብሔርበእሳት ነበልባል ይመጣል፤
ሠረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤
ንዴቱን በቍጣ፣
ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይገልጣል።
16 በእሳትና በሰይፍ፣
እግዚአብሔርፍርዱን በሰው ሁሉ ላይ ያመጣል፤
በእግዚአብሔርሰይፍ የሚታረዱት ብዙ ይሆናሉ።
17 “ወደ አትክልት ቦታዎች ለመሄድና ከተክሎቹ አንዱን ለማምለክ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የዕሪያዎችንና የዐይጦችን ሥጋ፣ የረከሱ ነገሮችንም የሚበሉ ሁሉ የመጨረሻ ፍርዳቸውን በአንድነት ይቀበላሉ” ይላልእግዚአብሔር።
18 “እኔም ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ መንግሥታትንና ልሳናትን ሁሉ ልሰበስብ እመጣለሁ፤እነርሱም መጥተው ክብሬንም ያያሉ።
19 “በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶባልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ።
20 ለእግዚአብሔርቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላልእግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቊርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል።
21 እኔም ካህናትና ሌዋውያን ይሆኑ ዘንድ አንዳንዶቹን እመርጣቸዋለሁ” ይላልእግዚአብሔር።
22 “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላልእግዚአብሔር፤
23 “ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል” ይላልእግዚአብሔር፤
24 “ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸው አይጠፋም፤ ለሰውም ዘር ሁሉ አስጸያፊ ይሆናሉ።”