የምስጋና መዝሙር
1 በዚያ ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፤
ብርቱ ከተማ አለችን፣
አምላካችን ቅጥሮቿንና ምሽጎቿን፣
ለድነት አድርጎአል።
2 በእምነቱ የጸና
ጻድቅ የሆነ ሕዝብ ይገባ ዘንድ፣
በሮቿን ክፈቱ።
3 በአንተ ላይ ታምናለችና፣
በአንተ የምትደገፈውን ነፍስ
ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
4 በእግዚአብሔርለዘላለም ታመኑ፤
ጌታእግዚአብሔርየዘላለም ዐምባ ነውና።
5 በከፍታ የሚኖሩትን ዝቅ ዝቅ ያደርጋል፤
ከፍ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፤
ወደ ምድር ይጥላታል፤
ከትቢያም ጋር ይደባልቃታል።
6 እግር፣
የተጨቋኞች እግር፣
የድኾች ኮቴ ይረግጣታል።
7 የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤
አንተ ቅን የሆንህ ሆይ፤
የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8 እግዚአብሔርሆይ፤ በሕግህጐዳና በመሄድ፣
አንተን ተስፋ አድርገናል፤
ስምህና ዝናህ፣
የልባችን ምኞት ነው።
9 ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፤
መንፈሴም በውስጤ ትፈልግሃለች።
ፍርድህ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ፣
የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።
10 ክፉዎች ርኅራኄ ቢደረግላቸው እንኳ፣
ጽድቅን አይማሩም፤
በቅንነት ምድር እንኳ ክፋትን ያደርጋሉ፤
የእግዚአብሔርንምግርማ አያስተውሉም።
11 እግዚአብሔርሆይ፤ ክንድህ ከፍ ከፍ ብሎአል፤
እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤
ለሕዝብህ ያለህን ቅናት ይዩ፤ ይፈሩም፤
ለጠላቶችህም የተዘጋጀው እሳት ይብላቸው።
12 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ሰላምን መሠረትህልን፤
የሠራነውንም ሁሉ አንተ አከናወንህልን።
13 እግዚአብሔርአምላካችን ሆይ፤
ከአንተ ሌላ ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤
እኛ ግን የአንተን ስም ብቻ እናከብራለን።
14 እነርሱ ሞተዋል፤ ከእንግዲህ በሕይወት አይኖሩም፤
መንፈሳቸው ተነሥቶ አይመጣም።
አንተ ቀጣሃቸው፤ አጠፋሃቸው፤
መታሰቢያቸውንም ሁሉ ደመሰስህ።
15 እግዚአብሔርሆይ፤ ሕዝብን አበዛህ፤
ሕዝብን አበዛህ።
ክብሩን ለራስህ አደረግህ፤
የምድሪቱንም ወሰን ሁሉ አሰፋህ።
16 እግዚአብሔርሆይ፤ በተጨነቁ ጊዜ ወደ አንተ መጡ፤
በገሠጽሃቸውም ጊዜ፣
በለሆሳስ ድምፅ ይጸልያሉ።
17 እግዚአብሔርሆይ፤ የፀነሰች ሴት ልትወልድ ስትል፣
በምጥ እንደምትጨነቅና እንደምትጮኽ፣
እኛም በፊትህ እንዲሁ ሆነናል።
18 አረገዝን በምጥም ተጨነቅን፤
ነገር ግን ነፋስን ወለድን፤
ለምድርም ድነትን አላመጣንም፤
የዓለምን ሕዝብ አልወለድንም።
19 ነገር ግን ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤
በድናቸውም ይነሣል።
እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣
ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ።
ጠልህ እንደ ንጋት ጠል ነው፤
ምድር ሙታንን ትወልዳለች።
20 ሕዝቤ ሆይ፤ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ፤
በርህን ከኋላህ ዝጋ፤
ቍጣው እስኪያልፍ ድረስ፣
ለጥቂት ቀን ተሸሸግ።
21 በምድር ላይ የሚኖረውን ሕዝብ ስለ ኀጢአቱ ለመቅጣት፣
እነሆ፤እግዚአብሔርከመኖሪያው ወጥቶ ይመጣል፤
ምድር በላይዋ የፈሰሰውን ደም ትገልጣለች፤
የተገደሉትንም ከእንግዲህ አትሸሽግም።